እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዘርፍ የስልጠና እና የምርምር የትኩረት መስኩ መሆነን አስታወቀ

ዩኒቨርሲቲው ከአማራ ክልል እውቅና የተሰጠውን የቱሪዝምና ሆቴል ማሰልጠኛና የምዘና ማዕከል ( Tourism and Hotel management Training and Competency Centre) መርቆ ስራ አስጀምሯል። በምረቃ ፕሮግራሙ የተገኙት የእንጅባራ ዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት (Tourism and Entrepreneurship Development) የቱሪዝም እና ስራ ፈጠራ ዘርፎች ከዩኒቨርሲቲው ዋና የትኩረት መስኮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የሆቴል እና ቱሪዝም ኢንዱስትሪን በማስተዋቀቅ፣ በማዘመን እና በማሳደግ አካባቢውን፣ ክልሉን እና አገሪቱን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል ። በአገራችን ቱሪዝም ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ እድገት ምሰሶዎች አንዱ ሆኖ መለየቱን፣ በቀጠናው ሰፊ እና ውብ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ የቱሪስት መስህቦች ያሉት እንዲሁም እንጅባራም የህዳሴ ግድብ መግቢያ በር (Gateway) መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የእንጅባራ ዩንቨርሲቲ ይህንን ከግምት በማስገባት ቱሪዝም አንዱ የትኩረት መስኩ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ጋርዳቸው አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማህበረሰብ በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ከመማር ማስተማር ባለፊ በሆቴል እና ቱሪዝም ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት የሚያግዝ የቱሪዝምና ሆቴል ማሰልጠኛና ምዘና ማዕከል በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መከፈቱን እና አገር አቀፍ ፋይዳ ያላቸውን ምርምሮች ለማከናውን እና የባለሙያ እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጋር የውል ስምምነት መደረጉንም ገልፀዋል ።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ይልቃል አንዱዓለም(ዶ/ር) እንደተናገሩት ቱሪዝምና ምቹ የሆቴል መስተንግዶ ከኢንዱስትሪዎች በላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ቱሪዝም ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ለመገንባትና የባህል ልውውጥን በማጎልበት ዘላቂ ልማትን ለማራመድ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ዶክተር ይልቃል አክለውም ማዕከሉ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉ አጫጭር ስልጠናዎች ለመስጠት የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት በማድረግ የአካባቢውን የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ለማዘመን እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም እና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዳዊት ጥላሁን እንደገለፁት እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ቱሪዝም እና ሆቴል ማኔጅመንት ዙሪያ ለተለያዩ ሆቴሎች እና ባለሙያዎች ስልጠናና ድጋፍ በመስጠት ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው የስልጠና እና የምዘና ማዕማዕከሉ ከአጫጭር ስልጠና በተጨማሪ በቱሪዝም እና ሆቴል ማኔጅመንት የብቃት ምዘና (COC) እንደሚሰጥ እና ይህ እውቅና ያለው የስልጠና እና የምዘና ማዕከሉ በአማራ ክልል በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ሲከፈት የመጀመሪያው መሆኑን ገልፀዋል ።

ህዳር 10/2017 ዓ.ም

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ