ህዳር 11/2017 ዓ.ም
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የምርምር ካውንስል አባላት የተሳተፉበት የስንዴ ምርጥ ዘር ብዜት ማሳ እና የድንች ምርጥ ዘር ማጎንቆያ ክፍል ጉብኝት ተከናውኗል። ዩኒቨርሲቲው ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክረምት እያከናወነ ከሚገባቸው ተግባራት መካከል ‹‹ደንደአ›› የተሰኘ ስንዴ ከምርምር ድርጅት መስራች(C1) በመረከብ በ6 ሄክታር ላይ እያባዛ እንዳለና ሰብሉም በጥሩ ይዞታ ላይ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው የእርሻ ፕሮጀክቶች አስተባሪና የዘር ብዜት መሪ አማረ አለምነው(ዶ/ር) በማሳ ጉብኝቱ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለአካባቢው ተስማሚና የተሻለ ምርት የሚሰጥ ‹‹በለጠ ›› የተሰኘ ድንች ዘር በ1.5 ሄክታር ላይ ለምቶ በማጎንቆያ ክፍል በርብራብ ለዘር ብዜት የተቀመጠን ድንችም አመራሩ እንዲገበኘው ተደርጓል፡፡
በጉብኝት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የእንጅባራ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጋርዳቸው ወርቁ በተመራማሪዎች እየተሰሩ ያሉት የምርምር ስራዎች እጅግ ተስፋ ሰጪ እና አበረታች መሆናቸውን ገልጸው ለተመራማሪዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ፕሬዚዳንቱ የገበሬው የምርጥ ዘር ፍላጎት በዩኒቨርሲቲው ብቻ እንደማይሟላ ገለጸው በሰፊው የምርጥ ዘር ብዜት ለማከናወን ከግብርና ምርምር፣ከሞዴል እርሶ አደሮች እና ከግብርና ጽ/ቤቶች ጋር በቅንጀት መስራት እንደሚያስፈልግ በጉብኝት ማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ አሳስበዋል።