ለኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የግብርና ናሙና ቆጠራ ሰልጣኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃግብር በእንጅባራ ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና ልማት ም/ፕሬዚደንት ወሀቤ ብርሃን(ዶ/ር) የግብርና መረጃዎችን ናሙና ለመሰብሰብ የሰለጠነ መረጃ ሰብሳቢ የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህ የስልጠና ፕሮግራም መዘጋጀቱን ተናግረው በግብርና ናሙና አወሳሰድ ላይ ወቅታዊ፣ ተጨባጭና ተዓማኒነት ያለውን መረጃ ለማሰባሰብ የተዘጋጀውን ስልጠና በትኩረት መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከ700 በላይ ሰልጣኞች መመደባቸውን ጠቅሰው በስልጠናው ሂደት ጊዜ አስፈላጊ የሆነ ዕውቀት እና ክህሎት በመያዝ ለግብርና ናሙና ጥናት የሚያስፈልገውን መረጃ በመሰብሰብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኣሳስበው የተሳካ የስልጠና ጊዜ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኞች በግቢ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ የሥነ ምግባር፣ የምግብ እና መኝታ የመሳሰሉት አገልግሎቶች አስመልክተው የአስተዳደር እና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ልዩ ረዳት የሆኑት አቶ ታደሰ ጥላሁን ገለጻ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለሙያ እና በእንጅባራ ዩኒቨርሰቲ የሰልጣኞች አስተባበሪ የሆኑት አቶ ረዳ ነጋሽ በበኩላቸው ስልጠናው ለተከታታይ 25 ቀናት በ12 ክፍሎች በብቁ አሰልጣኞች በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር ታግዞ እንደሚሰጥ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ላደረገላቸው አጠቃላይ ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ያለህን እምቅ አቅም ለይተህ ተጠቀም!
ነሐሴ 20/2016 ዓ.ም፤
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ